1 Samuel 25

ዳዊት፣ ናባልና አቢግያ

1ሳሙኤልም ሞተ፤ እስራኤል ሁሉ ተሰብስበው አለቀሱለት፤ አርማቴም ባለው ቤቱም ቀበሩት።

ከዚያም ዳዊት ተነሥቶ ወደ ማዖን ምድረ በዳ ወረደ።
2በማዖን ምድር በቀርሜሎስ ንብረት ያለው አንድ ባለጠጋ ሰው ነበረ፤ እርሱም አንድ ሺሕ ፍየሎችና በቀርሜሎስ የሚሸልታቸው ሦስት ሺሕ በጎች ነበሩት። 3የሰውየው ስም ናባል፣ የሚስቱም ስም አቢግያ ነበረ። እርሷም አስተዋይና ውብ ነበረች፤ ባሏ ግን ባለጌና ምግባረ ብልሹ ሰው ነበረ፤ እርሱም ከካሌብ ወገን ነበር።

4ዳዊት በምድረ በዳ ሳለ ናባል በጎቹን እንደሚሸልት ሰማ። 5እርሱም ዐሥር ወጣቶችን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ “ወደ ቀርሜሎስ ወደ ናባል ውጡ፤ በስሜም ሰላምታ አቅርቡለት። 6እንዲህም በሉት፤ ‘ዕድሜህ ይርዘም! ሰላም ለአንተ ይሁን፤ ሰላም ለቤተ ሰብህና የአንተ ለሆነው ሁሉ ይሁን።

7“ ‘በዚህ ጊዜ በጎች እንደምትሸልት ሰምቻለሁ፤ እረኞችህ ከእኛ ጋር በነበሩበት ጊዜ፣ ያደረስንባቸው ጕዳት የለም፤ ቀርሜሎስ በነበሩበት ጊዜ ሁሉ፣ የጠፋባቸው አንዳች ነገር አልነበረም። 8የገዛ አገልጋዮችህን ጠይቅ፤ እነርሱም ይነግሩሃል። ስለዚህ አመጣጣችን በጥሩ ቀን በመሆኑ፣ እነዚህ ወጣቶቼ በፊትህ ሞገስ ያግኙ። እባክህን ለአገልጋዮችህና ለልጅህ ለዳዊት የምትችለውን ያህል ስጥ።’ ”

9የዳዊት ሰዎች ከዚያ እንደ ደረሱም፣ በዳዊት ስም ይህንኑ መልእክት ለናባል ከተናገሩ በኋላ ምላሹን ይጠባበቁ ጀመር።

10ናባልም ለዳዊት አገልጋዮች እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ለመሆኑ ይህ ዳዊት ማነው? የእሴይስ ልጅ ማን ነው? በአሁኑ ጊዜ ከጌቶቻቸው የሚኰበልሉ አገልጋዮች ብዙ ናቸው። 11ታዲያ እንጀራዬንና ውሃዬን እንዲሁም በጎቼን ለሚሸልቱልኝ ሰዎች ያረድሁትን ፍሪዳ ከየት እንደ መጡ ለማይታወቁ ሰዎች የምሰጠውስ ለምንድን ነው?”

12የዳዊት ሰዎችም ወደ መጡበት ተመለሱ፤ እዚያም እንደ ደረሱ የተባሉትን ሁሉ ነገሩት። 13ዳዊትም ሰዎቹን፣ “በሉ ሁላችሁም ሰይፋችሁን ታጠቁ” አላቸው። ስለዚህ ሁሉም ሰይፋቸውን ታጠቁ፤ ዳዊትም የራሱን ታጠቀ። አራት መቶ ያህል ሰዎች ከዳዊት ጋር ሲወጡ መቶ ያህሉ ግን ጓዝ ለመጠበቅ ቀሩ።

14ከአገልጋዮቹ አንዱ ለናባል ሚስት ለአቢግያ እንዲህ አላት፤ “እነሆ፤ ዳዊት ሰላምታውን እንዲያቀርቡለት ከምድረ በዳ ወደ ጌታችን መልእክተኞች ልኮ ነበር፤ እርሱ ግን የስድብ ናዳ አወረደባቸው። 15እነዚህ ሰዎች ግን እጅግ መልካም ነበሩ፤ ጕዳትም አላደረሱብንም፤ በዱር አብረናቸው በነበርንበት ጊዜም ሁሉ፣ ምንም ነገር አልጠፋብንም። 16በጎቻችንን እየጠበቅን አብረናቸው ባሳለፍነው ጊዜ ሁሉ፣ ቀንም ሆነ ሌሊት በዙሪያችን ዐጥር ሆነውን ነበር። 17አሁንም በጌታችንና በመላው ቤተ ሰቡ ላይ መከራ እያንዣበበ ስለሆነ፣ አስቢበትና የምታደርጊውን አድርጊ፤ እርሱ እንደ ሆነ እንዲህ ያለ ባለጌ ሰው ስለሆነ፣ ደፍሮ የሚነግረው አንድም ሰው የለም።”

18አቢግያም ጊዜ አላጠፋችም፤ ሁለት መቶ እንጀራ፣ ሁለት አቍማዳ የወይን ጠጅ፣ አምስት የተሰናዱ በጎች፣ አምስት መስፈሪያ
37 ሊትር ያህል ነው።
የተጠበሰጠ እሸት፣ መቶ የወይን ዘለላና ዘቢብ፣ ሁለት መቶ ጥፍጥፍ የበለስ ፍሬ ወስዳ በአህዮች ላይ ጫነች።
19ከዚያም አገልጋዮቿን፣ “ቀድማችሁኝ ሂዱ፤ እኔም እከተላችኋለሁ” አለቻቸው፤ ለባሏ ለናባል ግን አልነገረችውም።

20እርሷም በአህያዋ ላይ ተቀምጣ ወደ ሸለቆው በምትወርድበት ጊዜ ዳዊትና ሰዎቹ ወደ እርሷ ወረዱ፤ እርሷም አገኘቻቸው። 21ዳዊትም እንዲህ ብሎ ነበር፤ “ምንም ነገር እንዳይጠፋበት የዚህን ሰው ሀብት በምድረ በዳ ያን ያህል መጠበቄ ለካ በከንቱ ኖሯል፤ ደግ በሠራሁ ይኸው ክፉ መለሰልኝ። 22ነገ ጧት የእርሱ ከሆነው ሁሉ አንድ ወንድ እንኳ በሕይወት ባስቀር እግዚአብሔር በዳዊት ላይ
አንዳንድ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕሞች ከዚህ ጋር ይስማማሉ፤ ዕብራይስጡ ግን በዳዊት ጠላቶች ላይ ይላል።
እንዲህ ያለውን ነገር ያድርግበት፣ ከዚህም የከፋ ይጨምርበት!”

23አቢግያም ዳዊትን ባየች ጊዜ ወዲያው ከአህያዋ ወርዳ፣ በዳዊትም ፊት በግምባሯ ተደፍታ እጅ ነሣች። 24በእግሩም ላይ ወድቃ እንዲህ አለች፤ “ጌታዬ ሆይ፤ በደሉ በእኔ ላይ ብቻ ይሁን፤ እባክህ አገልጋይህ ታናግርህ፤ የምትልህንም ስማ። 25ጌታዬ፣ ያን ባለጌ ሰው ናባልን ከቁም ነገር አይቍጠረው፤ ስሙ ራሱ ጅል ማለት ስለሆነ፣ ሰውየውም ልክ እንደ ስሙ ነው፤ ጅልነትም አብሮት የኖረ ነው። እኔ አገልጋይህ ግን ጌታዬ የላካቸውን ጕልማሶች አላየኋቸውም። 26ጌታዬ ሆይ፤ ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፤ ደም ከማፍሰስና በገዛ እጅህ ከመበቀል የጠበቀህ እግዚአብሔር ነው፤ አሁንም ጠላቶችህና ጌታዬን ሊጐዱ የሚፈልጉ ሁሉ እንደ ናባል ይሁኑ፤ 27አገልጋይህም ለጌታዬ ያመጣችው ይህ ስጦታ አንተን ለሚከተሉ ጕልማሶች ይሰጥ። 28ጌታዬ የእግዚአብሔርን ጦርነት ስለሚዋጋ እግዚአብሔርም ለጌታዬ ሥርወ መንግሥቱን በርግጥ ለዘላለም የሚያጸናለት በመሆኑ፣ እባክህ የእኔን የአገልጋይህን በደል ይቅር በል፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ ክፋት አይገኝብህ። 29ማንም ሰው ሕይወትህን ለማጥፋት ቢያሳድድህ እንኳ፣ የጌታዬ ሕይወት በሕያዋን አንድነት እስራት ውስጥ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ በሰላም ትጠበቃለች፤ የጠላቶችህን ሕይወት ግን፣ እንደ ወንጭፍ ድንጋይ ይወነጭፋል። 30እግዚአብሔር ለጌታዬ በሰጠው ተስፋ መሠረት በጎውን ነገር ሁሉ ባደረገለትና በእስራኤልም ላይ ባነገሠው ጊዜ፣ 31ጌታዬ የምታዝንበት ምክንያት ወይም የኅሊና ጸጸት አይኖርህም፤ በከንቱ ያፈሰስኸውም ደም ሆነ በገዛ እጅህ የተበቀልኸው የለምና። እግዚአብሔር በጎ ነገር ባደረገልህ ጊዜ እኔን አገልጋይህን ዐስበኝ።”

32ዳዊትም አቢግያን እንዲህ አላት፤ “ዛሬ እንድታገኚኝ ወደ እኔ የላከሽ፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን። 33ደም እንዳላፈስና በገዛ እጄ እንዳልበቀል ዛሬ ስለ ጠበቅሽኝ ስለ በጎ ሐሳብሽ አንቺም የተባረክሽ ሁኚ። 34ጕዳት እንዳላደርስብሽ የጠበቀኝ የእስራኤል አምላክ ሕያው እግዚአብሔርን! እንዲህ በቶሎ መጥተሽ ባታገኚኝ ኖሮ፣ እስኪነጋ ድረስ ለናባል አንድ ወንድ እንኳ ባልተረፈ ነበር።”

35ከዚያም ዳዊት ያመጣችለትን ከእጇ ተቀብሎ፣ “በሰላም ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ እነሆ፤ ቃልሽን ሰምቻለሁ፤ የጠየቅሽኝንም ተቀብያአለሁ” አላት።

36አቢግያም ወደ ናባል በተመለሰች ጊዜ፣ እነሆ፤ በቤቱ እንደ ንጉሥ ግብዣ ትልቅ ግብዣ አድርጎ አገኘችው፤ ክፉኛም ሰክሮ ልቡ በደስታ ተሞልቶ ነበር። ስለዚህ እስኪነጋ ድረስ ምንም አልነገረችውም። 37ነግቶ የወይን ጠጁ ስካር ካለፈለት በኋላ የሆነውን ሁሉ ስትነግረው ልቡ ቀጥ አለ፤ ሰውነቱም እንደ ድንጋይ በድን ሆነ። 38ዐሥር ቀን ያህል ካለፈ በኋላ፣ እግዚአብሔር ናባልን ቀሠፈው፤ እርሱም ሞተ።

39ዳዊትም ናባል መሞቱን በሰማ ጊዜ፣ “የናባልን ስድብ የተበቀለልኝና እኔን አገልጋዩን ክፉ ከማድረግ የጠበቀኝ እግዚአብሔር ይመስገን፤ ናባል የሠራውንም ክፉ ነገር በራሱ ላይ መለሰበት” አለ።

ዳዊትም አቢግያ ሚስት ትሆነው ዘንድ በመጠየቅ መልእክት ላከባት።
40አገልጋዮቹም ወደ ቀርሜሎስ ሄደው አቢግያን፣ “ሚስት ትሆኚው ዘንድ እንድንወስድሽ ዳዊት ወደ አንቺ ልኮናል” አሏት።

41እርሷም ተነሥታ በግምባሯ በመደፋት እጅ ከነሣች በኋላ፣ “እነሆ፤ እኔ ገረድህ አንተን ለማገልገል፣ የጌታዬንም አገልጋዮች እግር ለማጠብ ዝግጁ ነኝ” አለች። 42አቢግያም ወዲያውኑ በአህያ ላይ ተቀምጣ አምስት አገልጋዮቿን በማስከተል፣ ከዳዊት መልእክተኞች ጋር ሄደች፤ ለዳዊትም ሚስት ሆነችው። 43እንዲሁም ዳዊት ኢይዝራኤላዊቷን አኪናሆምን አገባ፣ ሁለቱም ሚስቶቹ ሆኑ። 44ሳኦል ግን የዳዊት ሚስት የነበረችውን ልጁን ሜልኮልን፣ ለጋሊም ተወላጅ ለሌሳ ልጅ ለፈልጢ ሰጥቶ ነበር።

Copyright information for AmhNASV